Friday, December 6, 2013

«እንጀራ ከአልጫ እና ከቀይ ወጥ ጋር ወይንም ሞት»








ከዳንኤል ክብረት
«እንጀራ ከአልጫ እና ከቀይ ወጥ ጋር ወይንም ሞት»
የዛሬ ሁለት ዓመት በ2000 ዓም ነው፡፡ የገና በዓል አልፎ በቀጣዩ እሑድ፡፡ ከዚህ በፊት አጋጥሞኝ የማያውቅ አንድ አዲስ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ጓጉቻለሁ፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት በተለያዩ መድረኮች ላይ የዐቅሜን ያህል «አስተምሬያለሁ»፡፡ የዚህኛው ግን ይለያል፡፡
በጠዋቱ ዲያቆን ምንዳየ ብርሃኑ ቤቴ ድረስ መጥቶ በመኪናው ይዞኝ ሄደ፡፡ ስለ መርሐ ግብሩ እየተነጋገርን እና ይህንን ዕድል በማግኘታችን ዕድለኞች መሆናችች እያነሣን በቀለበት መንገድ ከነፍን፡፡ መርሐ ግብሩን ለፈቀዱት የማረሚያ ቤት ባለ ሥልጣናትም ምስጋናችንን አቀረብን፡፡ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ እንዲህ ያለ የማናስበው ነገር በመደረጉ እዚህች ሀገር ውስጥ ሳናውቃቸው የተቀየሩ ነገሮች አሉ ማለት ነው) እያልን ነበር የምንጓዘው፡፡
እነሆ ቃሊቲ የሚገኘው ዋናው ማረሚያ ቤት በር ላይ ደረስን፡፡ እንደኛ ለመርሐ ግብሩ የተዘጋጁ እናቶች፣ እኅቶች፣ ወንድሞች አየን፡፡ ራቅ ብለው ደግሞ በወቅቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቡነ ይስሐቅ ከአንድ አባት ጋር መኪና ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡
ለመግባት የሚያስፈልገን ሂደት ተጠናቀቀና በብጹእ አባታችን መሪነት ወደ ውስጥ ገባን፡፡ እኔ በዚህ መልኩ ወደ ማረሚያ ቤት ስገባ የመጀመርያዬ ነበር፡፡ እያንዳንዷን ነገር በንሥር ዓይን ነበር የማያት፡፡ እየሄድኩ ያለሁት በታሪክ መንገድ ላይ ነበርና፡፡
አንድ ትልቅ በር ተከፈተልንና በፖሊሶቹ አስተናጋጅነት ወደ ውስጥ ዘለቀን፡፡ የፖሊሶቹ መስተንግዶ ለመስተንግዶ ተብለው በተቀጠሩት አስተናጋጆች ዘንድ እንኳን የማይገኝ ዓይነት ነበር፡፡
ገባን፡፡
ዙርያውን በተገጠገጠ ቤት የተከበበ ግቢ ነው፡፡ ቤቱ በአራት መዓዝን ሪጋ የተሠራ ነው፡፡ ከቤቱ ፊት ለፊት መሐል ሜዳውን ከብቦ የግቢ አትክልት አስውቦታል፡፡ መካከለኛው ሜዳ ጽድት ብሎ ማረሚያ ቤት መሆኑን ያስረሳል፡፡ በሜዳው መካከል በቆርቆሮ ተሠርቶ በመስተዋት የተዋበ፣ በመጋረጃም የተጋረደ ሥዕል ቤት አለ፡፡
እኛ ስንገባ አንድ አረጋዊ ሰው ሄደው መጋረጃውን ገለጡት፡፡ አቡነ ይስሐቅ እንደ ቆሙ ጸሎት አደረሱ፡፡ ሁሉም በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡ ጸሎቱ እንዳበቃ በተዘጋጀልን መቀመጫ ተቀመጥን፡፡ ምንዳዬ ከአቡነ ይስሐቅ ጎን፣ እኔም ከምንዳዬ ጎን ተቀመጥን፡፡
በዚህ ጊዜ ጋቢ የለበሱ እና መቋሚያ የያዙ አንድ አዛውንት ከጎኔ መጥተው ቁጭ አሉ፡፡ ልቤ አንዳች ነገር ያወቀ መሰለው፡፡ መርሐ ግብሩን ያስተናግድ የነበረውን ልጅ ጠራሁትና በኋላዬ በኩል ጠየቅኩት፡፡ በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ፡፡
ክው አልኩ፡፡
ከጎኔ የተቀመጡትን ሰው ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ማየቴ ነው፡፡ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ባደግኩበት አካባቢ መጥተው ነበር፡፡ ያኔ ሲመጡ የሙዚቃ አስተማሪያችን የሰልፍ መዝሙር አስጠንተውን በከተማዋ መግቢያ መንገድ ላይ ተሰልፈን ነበር የተቀበ ልናቸው፡፡ እጅግ ብዙ መኪኖች ተከታትለው አልፈው መዝሙራችንን አበቃን፡፡ የተቀበልናቸው ሰው ማንኛው እንደሆኑ ለማየት አልቻልንም ነበር፡፡ ብቻ ስማቸውን በተከ ታታይ ሰምተናል «ጓድ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ» እየተባለ ሲነገር፡፡
እነሆ አሁን ከጎኔ የተቀመጡት እርሳቸው ናቸው፡፡ በቴሌቭዥን አይቻቸው ዐውቃለሁ፡፡ የዛሬው ግን የተለየ ነበር፡፡ ወተት የመሰለ ነጭ ጋቢ ለብሰው፤ ወዝ የጠገበ መቋሚያ ይዘዋል፡፡ ትንሽ እንደማመም ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ በግራ እጃቸው የተደጎሰ ዳዊት አለ፡፡
ምንዳዬ መዝሙር ሲዘምር ፍቅረ ሥላሴም አብረው ይዘምሩ ነበር፡፡ ምን እርሳቸው ብቻ፣ ለገሠ አስፋው፣ ፍሥሐ ደስታ፣ ሌሎቹም ሁሉ እያሸበሸቡ እና እያጨበጨቡ አብረውት ነበር የሚዘምሩት፡፡ እነዚህ ትናንት ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩ፤ በተለየ ታሪካቸው የምናውቃቸው፤ ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር በዘመናቸው የተፈጸመ፡፡ በብዙ የሀገሪቱ መከራዎች ወስጥ ተጠያቂዎች የሆኑ ሰዎች ዛሬ ስታዩዋቸው እንደዚያ አይደሉም፡፡
የበዓሉ መዓድ ከመቆረሱ በፊት ጸሎት ተደርጎ ነበር፡፡ መጀመርያ ውዳሴ ማርያም ተደገመ፡፡ እኛ አይደለንም የደገምነው፡፡ መቋሚያቸውን ተደግፈው እነዚህ ታላላቅ የደርግ ባለ ሥልጣናት ናቸው የደገሙት፡፡ በአማርኛ እንዳይመስላችሁ፤ በግእዝ፡፡ የኪዳኑን ጸሎት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚቀበሉት እነርሱ ነበሩ፡፡
ትምህርት ሲሰጥ ሁሉም ጎንበስ ብለው ያነቡ ነበር፡፡ እኔ ከአሥራ አምስት ደቂቃ በላይ ማስተማር አልቻልኩም፡፡ የእነዚያን ሰዎች ዕንባ አይቼ መቆም አቃተኝ፡፡ ምናልባት እኛ ይቅር አላልናቸው ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን መሐሪ ነውና ይቅር እንዳላቸው ርግጠኛ ነበርኩ፡፡ በየቀኑ ኪዳን ይደረሳል፡፡ ዳዊት ይደገማል፡፡ ካህን አላቸው፡፡ ንስሐ ገብተዋል፡፡ ብዙዎቹ ቆራቢዎች ናቸው፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት በዚህ መልኩ እግዚአብሔርን ተማጽነዋል፡፡ ታድያ እግዚአብሔር ዝም ይላል እንዴ፡፡
ምን ብዬ ላስተምራቸው? ኑሮ ራሱ አስተምሯቸዋል፡፡ ሕይወት ራሱ ለውጧቸዋል፡፡ ድምፁን ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ ሰምተውታል፡፡ መስማትም ብቻ ሳይሆን አይተውታል፡፡ በየቀኑ ከእርሱ ጋር ይነጋገራሉ፤ እና ምን ልበላቸው? ኑሮውም፣ ጤናውም፣ ሃሳቡም አስረጅቷቸዋል፡፡
እነሆ ይህ ሥዕል በአእምሮዬ ተቀርጾ ይኖር ስለነበር በየጊዜው እነዚህ ሰዎች ይቅርታ ሊደረግላቸው ይገባል እያልኩ እንድናገር አድርገውኛል፡፡ አሁን ደግሞ መልካም ዜናዎችን እየሰማን ነው፡፡
ይህንን ነገር ላደረጉ የእምነት ተቋማት፤ በጎ ፍቃደኛነቱን ላሳየው መንግሥት፣ ተባባሪ ሆነው ታሪክ እየሠሩ ላሉ ተጎጅዎች የምናመሰግንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
እዚህ አሜሪካ ከመጣሁ ጀምሮ በየሬዲዮው፣ ፓልቶኩ፣ ዌብ ሳይቱ፣ ክርክሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሆኗል፡፡ ከሀገር ቤት እየደወሉ የሚከራከሩም ሰዎች አሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ «የምንፈልገውን ሁሉ ካላገኘን ምንም ነገር ባናገኝ ይሻላል» የሚል ዓይነት ክርክር እሰማለሁ፡፡ ዕርቁ እገሌን እና እገሌን የማያካትት ከሆነ፤ እነ እገሌም ካልተጨመሩበት ባይፈቱ ይሻላል ይባላል፡፡ ጎበዝ በዚህ ሁኔታ ስንናገር እግራችንን በተጎጅዎች መሬት ላይ እና በእሥረኞቹ መሬት ላይ ማቆም አለብን፡፡
«ወይ መሬት ላይ ያለ ሰው» አለ፡፡
የእነርሱ በዚሀ ሁኔታ ካለቀ የነ እገሌም ይጨመርበት ይባላል እንጂ «እንጀራ ስትሰጡኝ ከቀይ ወጡ ጋር አልጫ ከሌለው ረሃብ ይሻላል» ይባላል እንዴ፡፡ መጀመርያ ለእንጀራው እና ለቀይ ወጡ እናመስግን፤ ከዚያ ደግሞ አልጫ እንዲጨመር እንጠይቅ፡፡ «እንጀራ ከአልጫ እና ከቀይ ወጥ ጋር ወይንም ሞት» የሚለው መፈክር አሁንም አልለቀቀንም እንዴ፡፡
የይቅርታውን ሂደት የሚያከናውኑትን የሃይማኖት ተቋማትም ማመስገን፤ በርቱ ሥራችሁ የሚያስመሰግን ነው ብሎ ማበረታታት ይገባል፡፡ ባጠፉበት የምንወቅሳቸውን ያህል ሲያለሙ ማመስገን አለብንኮ፡፡ እናንተ ማን ናችሁና ይህንን ታደርጋላችሁ? እያሉ መራቀቅ ከአእምሮ ጅምናስቲክ ያለፈ ዋጋ የለውም፡፡ ማሩ ንጹሕ ነወይ? ከማለት ይልቅ ማሩን ማን አመጣው? እያሉ መወዛገብ በኅሊና ላይ ሌላ እሥር ቤት መክፈት ነው፡፡
በጎን ነገር ማንም ይሥራው፤ ከቻለ ሰይጣንም ይሥራው፤ ከሠራው ይደነቃል፣ ይመሰገናል፤ እነዚህ ተቋማት የሚችሉትን ሁሉ አድርገው እውነት እንደተባለው የይቅርታው ሂደት ከተከናወነ እሥረኞቹ ብቻ ሳይሆኑ እነርሱም ናቸው ከስንፍና የሚፈቱት እና ልናግዛቸውም፣ ልናደንቃቸውም ግድ ይለናል፡፡
መንግሥትም ቢሆን ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ይህንን ታሪክ በይቅርታ እና በዕርቅ ለመዝጋት በጎ ፈቃድ ካሳየ እሰዬው ነው፡፡ አጠፋ ሲባል ባገኘነው መንገድ ሁሉ ለመውቀስ የምንተጋ ሰዎች ሲያለማ ደግሞ ለማመስገን መሽቀዳደም አለብን፡፡
ግማሽ ብርጭቆ ውኃ የያዘውን ብርጭቆ ከየት በኩል ነው ማየት ያለብን? ለመሆኑ ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ ነው ወይስ ግማሽ ጎደሎ?
አንዳንድ ጊዜ ዕንቁላሉን ተከባክቦ፣ ሙቀት ሰጥቶ እና ከድመት ጠብቆ ዶሮ እንዲሆን ከመርዳት ይልቅ «እኔ ዶሮ ነበር የምፈልገው» እያሉ ዕንቁላሉን የመስበር አባዜ ያለብን ይመስላል፡፡ የተገኘውን በጎ ነገር ይዞ፣ እርሱን አጎልብቶ፣ የቀረውን ችግር ለመፍታት ከመጓዝ ይልቅ ያለውንም አጠፋፍቶ በዜሮ መጫወት ምን ይሉታል?
የተጎጅ ቤተሰቦች ይህንን ታሪካዊ ሥራ ለመሥራት ስትነሱ ሕመማችሁን እናውቃለን፤ ጉዳታችሁም ይሰማናል፡፡ ከእኛ ይልቅ ለእናንተ ሁኔታው ከባድ ነው፡፡ ግን እየሠራችሁ ያላችሁት የጀግንነት ሥራ ነውና እናደንቃችኋለን፡፡ በእምነት ጽድቅ፣ በታሪክ ክቡር፣ በባህል ምስጉን የሆነ ሥራ ነውና በርቱ፡፡
የዕርቁን ሂደት የምታከናውኑ የእምነት ተቋማትም ይህንን ነበርና ስንጠብቅባችሁ የኖር ነው ይበልጥ አጠናክራችሁ ቀጥሉ፡፡ መጀመርያ የጀመራችሁትን ለፍጻሜ አድርሱ፡፡ ከዚያ ደግሞ የሚቀራችሁን ትሠራላችሁ፡፡ ከምትሰሙት ይልቅ የምትሠሩት ውጤት ያመጣልና ወደ ኋላ አትበሉ፡፡
መንግሥትም ይህንን ታሪክ ሀገርን በሚያኮራ፤ ወገንን በሚያረካ እና ስማችንን በዓለም ላይ ከፍ በሚያደርግ መልኩ ለመዝጋት ያሳየኸውን በጎ ፈቃድ ለውጤት አብቃው፡፡ ሌሎች መሠራት ያለባቸው፤ መሆን የነበረባቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆናል፡፡ አሁን ግን እየሆነ ካለው ነገር እንነሣ፡፡ ምናልባት ይህ ታሪክ በራሱ ታሪክ ከመሆኑም በላይ ለሌላውም ታሪካችን በር የሚከፍት ታሪክ ሊሆን ይችላልና፡፡
የተጀመረው ይሳካ፣ ያልተጀመረውም ይቀጥል፡፡
ሁላችሁም እባካችሁ ክርክሩ ሰኞ ዕለት አልቆ ውዳሴውን ለመስማት አብቁን፡፡

No comments:

Post a Comment