Thursday, December 19, 2013

ኦባንግ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጋር ተነጋገሩ

http://www.goolgule.com/obang-spoke-with-south-sudan-foreign-affairs-minister/

“በራችሁን ዘግታችሁ እርቅ አውርዱ”
Picture2
* “ባለውለታችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ አዝኖባችኋል፣ አርቃችሁ እዩ”
“በትግሉ ወቅት ለነጻነት ስትዋደቁ ኢትዮጵያ በጋምቤላ አኙዋክ ምድር ላይ ሙሉ ከለላና ዋስትና በመስጠት ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሚረሳ ነው? ከነጻነት ታጋዮችችሁ ጎን በመሰለፍ ብረት ያነሱ የአኙዋክ ኢትዮጵያውያን ልጆች መስዋዕትነት ይዘነጋችኋል? አሁን ድረስ የትግሉ የመስዋዕትነት ቁስላቸው ያልዳነ የአኙዋክ ልጆች እንዳሉ ትዘነጋላችሁ?” በማለት የተናገሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ /ጥቁሩ ሰው/ ናቸው።
በታላላቅ መድረኮችና በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተሰሚነታቸውና ስብዕናቸው እየጎላ የሄደው ጥቁሩ ሰው ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ከላይ የተገለጸውን ህሊና የሚፈታተን ጥያቄ ያቀረቡት ለደቡብ ሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን ነው። ለረዥም ሰዓት ጊዜ ወስደው ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ የጎልጉል የአሜሪካ ዘጋቢ እንደዘገበው አቶ ኦባንግ ዶ/ር ባርናባን ያገኟቸው አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ነበር።
በጁባ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ ይፋ ከተደረገበት አንድ ቀን በፊት አስቀድሞ በተያዘ የውይይት መርሃ ግብር የተገናኙት ዶ/ር ባርናባና አቶ ኦባንግ በርካታ ወቅታዊ ጉዳዮችን አንስተው መነጋገራቸው ታውቋል። አቶ ኦባንግ የደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል ወቅት ኢትዮጵያ በመንግስት ደረጃ የሰጠችውን ሙሉ ድጋፍና፣ ድንበር ሳይከልላቸው በሁለቱም አገራት የሚገኙት የአኙዋክ ልጆች ትግሉን የነፍስ ዋጋ በመክፈል መደገፋቸውን በማስታወስ በውይይቱ ወቅት ያነሱት ያለ ምክንያት አልነበረም።
“በጆን ጋራንግ ይመራ የነበረው ትግል ፍሬ አፍርቶ ደቡብ ሱዳን ነጻ ስትወጣ የማይረሳ ውለታ ለሰራቸው ኢትዮጵያና የአኙዋክ ልጆች የተከፈላቸው ብድር አሳዛኝና የወደፊቱን ጊዜ ያላገናዘበ ነው” በማለት በውይይቱ ስለተነሱ ነጥቦች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኦባንግ፣ “ለህዝቦች ነጻነትና ለሰብአዊ መብት መከበር የታገለ ድርጅትና አመራሮች ለነጻነታቸው የተከፈለላቸውን የደም ዕዳ ያወራረዱትና እያወራረዱ ያሉት ከወያኔ መሪዎች ጋር በማበር ከለላ የጠየቁ ህጋዊ ስደተኞችን እያፈኑ ለወያኔ አሳልፎ በመስጠት መሆኑ አሳዝኖኛል። ኢትዮጵያዊያን አዝነዋል” በማለት ነበር።
ህጋዊ ከለላ የጠየቁ ስደተኞች ቶርቸር እንዲደረጉ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲታሰሩና ኢሰብአዊ ግፍ እንዲፈጸምባቸው ለአምባገነኖች አሳልፎ መስጠት ዘግይቶም ቢሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል አቶ ኦባንግ አስረግጠው ተናግረዋል። በ1993 የአኙዋክ ጄኖሳይድ /የጅምላ ጭፍጨፋ/ ሸሽተው በስደት ደቡብ ሱዳን የገቡ የአኙዋክ ልጆችን ለገዳዩ የወያኔ አንጋች ሃይል ማስረከብ መቆም እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ኦባንግ “ይህንን ተግባር የፈጸሙትም ቢያንስ ዓለም አቀፋዊውን ህግ ተላልፈዋልና ሊጠየቁ ይገባል። እርስዎም ይህንኑ የማስፈጸም ሃላፊነት ይኖርብዎታል” በማለት ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የአኙዋክና የበኩር ልጆችና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት ከድንበር ያለፈ የደም ትስስርና ኢትዮጵያ የማይረሳ ውለታ በመክፈል ያከበረችው ውህደት በመሆኑ መንግስታቸው ቆም ብሎ ሊያስብ እንደሚገባው አቶ ኦባንግ ምክር አዘል መልዕክት ማስተላለፋቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ አስተማማኝ ከለላና ዋስትና በመስጠት የፈጸመችውን ሊዘነጋ የማይችል ተግባር አለማክበር ለወደፊቱ ወዳጅ የሚያሳጣ ብድር ለራስ የማስቀመጥ ያህል እንደሆነም በወጉ እንዲገነዘቡ ሚኒስትሩን ተማጽነዋል።
photoአምባገነኑና በህዝብ የሚጠላው የህወሃት አገዛዝ እድሜ አሁን ካለው ትውልድ እድሜ በላይ ዘሎ የሚሄድ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማቅረብ፣ መተዋወቅና መልካም ግንኙነት መመስረት ለወደፊቱ ጠቃሚ መሆኑንም አስረድተዋል። እርሳቸው በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄም /አኢጋን/ ከተመሰረተበት ዓላማ አንጻር የደቡብ ሱዳን መንግሥት ህወሃት/ኢህአዴግን ለማስደሰት ሲል ኢትዮጵያዊያን ላይ ፈጸመውና እየፈጸመ ባለው ተግባር ያዘኑ ወገኖች የቀድሞውን የፍቅር መንገድ እንዲከተሉ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ሕዝብ ያልወደደው መንግስትና ህዝብ ያልተቀበለው ኢንቨስትመንት መጨረሻው ኪሳራ በመሆኑ የደቡብ ሱዳን መንግስት ሊጠነቀቅ እንደሚገባው አቶ ኦባንግ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል። ከደቡብ ሱዳን ተነስቶ በጋምቤላ አድርጎ ወደ ኬኒያና ጅቡቲ ይዘረጋል የተባለው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ሕዝብን በመግፋትና በመበደል ከቶውንም ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ያለማቅማማት ጠቁመዋል።
ህዋሀት በጋምቤላ ንጹሃንን ከቀያቸው በጠመንጃ ሃይል በማባረር፣ መሬታቸውን በሳንቲም ቸብችቦ፣ የህይወታቸው ዋስትና የሆነውን ደናቸውን አስጨፍጭፎ፣ ለምን በማለት የጠየቁትን አስሮና ገድሎ ያቋቋመው ኢንቨስትመንት በዜሮ መጣፋቱን ለአብነት ጠቅሰው ማስረዳታቸው የጠቆሙት ጥቁሩ ሰው “ኢንቨስትመንት መልካም ነው። ህዝብ ካልተቀበለው ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ህዝብ ይሁንታ የማይሰጠው ኢንቨስትመንት ፍሬ አያፈራም። ከውስጥም ከውጪም ያላችሁን ግንኙነት መርምሩ። ያዘኑባችሁ ተበራክተዋል” ሲሉ መክረዋል።
በአዲስ የምትቋቋመው “አዲሲቷ ኢትዮጵያ” ለደቡብ ሱዳን ወንድምና እህቶች ጭምር ቦታ በማዘጋጀት መሆኑንን አቶ ኦባንግ አረጋግጠው “በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዲሞክራሲ መከበርና ለነጻነት በተከፈለው መስዋዕት የተገኘውን ድል የደቡብ ሱዳን መንግስት በአግባቡ እየተጠቀመበት አለመሆኑን አቶ ኦባንግ ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል። አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ከድል በኋላ የትግሉን መሐላ ሙሉ በሙሉ ረግጣለች በማለት መሪዎቹን ወቅሰዋል።
ከድል በኋላ በደቡብ ሱዳን በርካታ ችግሮች መከሰታቸውን በመዘርዘር የማስጠንቀቂያ ምክር መሰንዘራቸውን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አሁን ባለው ሁኔታ በደቡብ ሱዳን ባሉ ሃያ አንድ ጎሳዎች መካከል ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም። ስለዚህ በራችሁን ዘግታችሁ እርቅ አውርዱ። በቀደሙት ሰማዐታቶች ደምና አጥንት ላይ ዴሞክራሲን መስርቱ። ይህንን ካላደረጋችሁና አሁን በያዛችሁት የአምባገነንነትና የአንድ ሰው ወይም ጎሣ የበላይነት መንገድ ከቀጠላችሁ ጣጣው ወደኛም ያመራል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አስጠንቅቀዋቸዋል። አሁን ያለው የውስጥ ሽኩቻ መልኩን ሳይቀይር መፍጠን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋቸዋል። (አቶ ኦባንግ ይህንን ለውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ የተናገሩት እሁድ መፈንቅለ መንግሥት ከመሞከሩና አሁን ደግሞ በዘር /ጎሣ/ መስመር ተከፋፍለው ደቡብ ሱዳናውያን መጫረስ ከመጀመራቸው አንድ ቀን በፊት ነበር)
ambassador 1
አቶ ኦባንግ በአሜሪካ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጋር
በደቡብ ሱዳን እውነተኛ እርቅ ለማውረድ የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት አንድ ግብረ ሃይል ወደ ጁባ እንደሚልክ መረጃ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ኦባንግ በውይይቱ ወቅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀና ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክተዋል። በመጨረሻም አቶ ኦባንግ የሚመሩት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የእርቅ ደጆች የሚከፈቱበት አግባብ ላይ ከሚመለከታቸው ተጽዕኖ አድጊራዎችና አቅሙ ካላቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል። በማያያዝም “እኛ ሩቅ እያየን እየሰራን ነው። እኛ በስፋት እያሰብን በመራመድ ላይ ነን። በስፋት አስበን፣ ሩቅ እያየን ስንሰራ እናንተንም አንዘነጋም። በተቃራኒው እናንተ ለነጻነታችሁ የተዋደቁላችሁን የራሳችሁን ዜጎች እያነቃችሁ ለወያኔ አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ። ደም ያፈሰሱላችሁንና አጥንታቸውን የከሰከሱላችሁን ውድ ዜጎች ሳትታረቁ በምድራቸው ላይ ቱቦ ዘርግታችሁ ብር ልታመርቱ ታቅዳላችሁ። ይህ ከቶውንም ጤነኛ አካሄድ አይደለምና ህዝብን አስቀድሙ። አብረን እንስራ። ይህ መልካም ጅምር ነው” በማለት መሰናበታቸውን አቶ ኦባንግ ለጎልጉል ተናግረዋል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክትር አቶ ኦባንግ ሜቶ ከደቡብ ሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ጋር ለመወያየት የቻሉት ሚኒስትሩ አሜሪካ ከመምጣታቸው በፊት በኤምባሲያቸው አማካይነት አስቀድሞ በተያዘ መርሃ ግብር መሰረት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሩ ስለ ሰጡት አስተያየትና ምላሽ አቶ ኦባንግ በዝርዝር ለመናገር አልፈለጉም። አቶ ኦባንግ በትውልድ አኙዋክ ቢሆኑም እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት /አኢጋን/ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጭ በስደት በሚሰቃዩበት ቦታ ዘር፣ ቀለም፣ ጎሣ፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ሳይለይ ፈጥኖ በመድረስ እርዳታ በማድረግ እርሳቸውም በተመሳሳይ ተግባር ተጠምደው በቅንነት በማገልገል እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የእርቅ ደጆች እንዲከፈቱ አግባብ ካላቸውና አቅሙ ካላቸው ክፍሎች ጋር እየሰራን ነው በማለት አቶ ኦባንግ ለሚኒስትሩ የገለጹላቸውን ሃሳብ እንዲያብራሩ ከጎልጉል ተጠይቀው “ሁሌም የእርቅ ደጆች እንዲከፈቱ እንሰራለን። ይህ የጋራ ንቅናቄውና አርቀው የሚመለከቱ ዜጎች ሁሉ እምነት ነው። ብዙ ስራ እየሰራን ነው። ስንጨብጠውና ለህዝብ ሪፖርት የምናቀርብበት አሳማኝ ጊዜ ላይ ስንደርስ ብቻ ይፋ እናደርጋለን። ስራው በባህሪው ከንግግር በመቆጠብ ተግባር ላይ ማተኮርን ስለሚጠይቅ እኛም ባናወራው ጊዜው ሲደርስ ሁሉም በየፊናው የሚገልጸው ይሆናል። ስራው ሳይሰራ ፕሮፓጋንዳው ከቀደመ በሁሉም ወገን ተዓማኒነትን የማጣትና የመጣል አደጋ አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ ተግባር የናፈቀው ይመስለኛል” የሚል ድፍን መልስ ሰጥተዋል።
 POSTED BY SAMUALE TEWELDE

Tuesday, December 17, 2013

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የተመሰረተበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

December 17, 2013

ታህሳስ 7  2006 ዓም የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ከተመሰረተ  አንድ አመት ሞላው። አንድ አመት  በጭንቅና  በአሳር  ለተያዘች የዛሬይቱ ኢትዮጵያና ህዝቧ እጅግ ረጅም ግዜ እንደሆነ ህዝባዊ ሃይሉ በሚገባ  ይገነዘባል። ባላፈው አንድ አመት ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የመከራ የአሳርና የውርደት ህይወት ይበልጥ እየሰፋ፣ የሚፈጸምበት ግፍ ይበልጥ እየገዘፈ መሄዱን አይተነዋል። በሃገርና በህዝብ ላይ እየወረደ ያለውን ወያኔ ወለድ የስቃይና የፍዳ ናዳ በቅጡ ላጤነው  ሃገሪቱና ህዝቧ የአዳዲስ የስቆቃና የመከራ አይነቶች መፈተኛ ቤተ ሙከራዎች እየተደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር አይኖረውም። ለሚራበው ለሚረገጠው በግፍ ለታጎረው፣ በኑሮ ውድነት ለሚጠበሰው፣ ለተሰደደው ለተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ እንድ አመት በሲኦል የቀናትና የወራት መቁጠሪያ እንደሚለካ ዘመን እጅግ የረዘመ የስቃይ ግዜ ነው።Ginbot 7 Popular Force logo
የዋልድባ መነኩሳት ገዳማችን  አትድፈሩ አታፍረሱ በማለታቸው እየተገረፉ ለዘመናት ፈጣሪያቸውን ከሚማጸኑበት ለሃገርና  ለህዝብ ምልጃ ከቆሙበት ገዳም በዘር መመዘኛ እየተለዩ  እንደቆ ሻሻ ተጠርገው የተባረሩበት ፣ እምነታችን አትንኩ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችና  መሪዎቻቸው በሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው  ወህኒ መውረዳቸው አንሶ  ወንድሞቻችን ይፈቱ በማለት  ሰላማዊ  ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖቻቸን በወያኔ ነፍሰ- ገዳዮች  በአረመኔያዊ ጭካኔ የተጨፈጨፉት በዚሁ አመት ነው። ወያኔ በህዝብ መሃከል በዘራው የዘር መርዝ የተነሳ በሽዎች የሚቆጠሩ አማሮች ከጉራ ፈርዳና ከቤንሻንጉል፣ ኦሮሞዎች ለዘመናት ከኖሩበት ምስራቅ ሃረርጌ  አካባቢ  እንዲፈናቀሉና በገዛ ሃገራቸው መድረሻ ቢሶች  እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ አንድ አመት ውስጥ ነው። ጋምቤላዎች ሙርሲዎች አፋሮችና ሌሎችም ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች የተጨፈጨፉበት፣በልማት ስም ለመጡ የውጭ ወራሪዎችና ወያኔ ለፈጠራቸው ቱጃሮች ቦታ እንዲለቁ ተደርጎ ቀደምቶቻቸው ለዘመናት ከኖሩባቸው ቀየዎች እንዲነቀሉ ተደርገው እንደ አልባሌ ነገር የትም እንዲበተኑ የማድረጉ ሂደት ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ የቀጠለው በዚሁ አመት ነው። በዚሁ አንድ አመት በወያኔ የሃገሪቱ ገዥዎች በህዝብ ላይ የተፈጸመው  ጭካኔና ወንጀል ተዘርዝሮ  የሚያልቅ አይደለም።
ይህ ወያኔ  ሰራሽ ሃገር በቀል የውርደትና  የስቃይ ህይወት አልበቃ  ብሎ ወያኔ ከሳውዲ የጨለማ ዘመን ገዥዎች ጋር በመተባበር ወንድሞቻችን በሳውዲ አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዲታረዱ እህቶቻችን በቡድን በተደራጁ የሳውዲ ጎረምሳዎች  እንዲደፈሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ  ለኢትዮጵያውያን ያለውን እጅግ የከረረ ጥላቻ በአደባባይ ያሳየበት አመት ነው። እንዲህ አይነቱ የጅምላ ግፍና  ውርደት ከመከሰቱ በፊት ህዝባዊ ሃይሉ በአረብ ሃገር በባርነትና  በስደት የሚገኙ እህትቶቻችንን ወንድሞችችን ስቃይ  ስቃዩ አድርጎ በመውሰድ “ላንቺ ነው” በሚለው ድርጅታዊ መዝሙሩ “በባለጌ  አረቦች መዳፍ ውድ ክብራቸው ለጎደፈው እህቶቻችን፣ በአረቦች የባርነት ቀንበር ጀርባቸው ለጎበጠው  ወገኖቻችን እንደርስላችኋለን፣ የተሰባሰብነው  ደማችን የሚፈሰው የመከራ ቀናችሁን ለማሳጠር ነው” የሚል ቃል ኪዳኑ ሰጥቶ  ነበር። የድርጅታችንን ምስረታ አንደኛ  አመት ስናከብር ልባችንን ደስታ ሳይሆን ሃዘን እንዲሞላ የሚያደርገው ይህ ቃል ኪዳናችን ለማክበር የጀመርነው ጉዞ ከድርጅት ምስረታና ከድርጅታዊ ዝግጅት አልፎ   በኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና ንቀት  የተነፋውን የወያኔን እብሪት በማስተንፈስ የወሰዳቸው ተጨባጭ የአለኝታነት እርምጃዎች ባለመኖራቸው ነው።
ምንም እንኳን ግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል እራሱን እንደ ድርጅት አቁሞ  ኢትዮጵያውያንን አሰባስቦ  መራራው ትግል የሚጠይቀውን የፖለቲካ  የወታደራዊ ስልጠናና ትጥቅ አስታጥቆ  በወያኔ  ላይ ለመዝመት የጀመረውን ጉዞ የሚያስቆመው ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ብናውቅም የህዝብ ስቃይ ለግዜው መቀጠሉ የህባዊ ሃይሉን አባላት ማሰቃየቱ አልቀረም። በወያኔ  ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው ወገናችን ህዝባዊ ሃይሉ የወያኔን አገዛዝ እድሜ  የሚያሳጥሩ ፈጣን እርምጃዎችን እንዲወስድ በከፍተኛ  ጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ  እናውቃለን። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች በተጠንቀቅ እንደቆሙ እናውቃለን። እነዚህ ዜጎች ከሁሉም የእምነት የቋንቋ  የጾታ የእድሜ  የኑሮና  የማህበረሰብ ስብጥር የሚያካተቱ  እንደሆኑ እናውቃለን። በሃገሪቱ ታሪክ ተሰምቶና  ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ  የወታደር ልብሱን  እየጣፈ እንዲለብስ፣  የወታደር ጫማውን መቀየሪያ አጥቶ  ሸበጥ እንዲያደርግ የተገደደውን፣  የወያኔ ጀነራሎች በስልጣንና  በዘረፋ ሲያብጡ በድህነት እንዲሟሽሽ የተፈረደበት የሃገሪቱ ሰራዊት በዘር በእምነት ሳይለያይ ከህዝባዊ ሃይሉ ጎን ለመቆም አሰፍስፎ  የቆመ  እንደሆነ  እናውቃለን። ይህ ሃገራዊ እውነታ ለህዝብ የገባነውን ቃልኪዳን የለምንም ጥርጣሬ  ማስከበር እንደምንችል በሙሉ ድፍረት እንድናውጅ የሚያስችለን ሃቅ ነው።
የወያኔ ጀንበር እየጠለቀች የኢትዮጵያ  ህዝብ ጀንበር እየፈካች የመሄዱ ጉዳይ እንደማይታጠፈው  የመንጋትና  የመምሸት የተፈጥሮ ህግ ነቅነቅ የማይል እንደሆነ ግንቦት7 ጠንቅቆ ያውቃል።  እውቀታችን ልዩ ጥበብ የሚጠይቅ ኣይደለም። ግፍ ፍትህን አሸንፎ፣ እውነት በሃሰት ተደፍቃ፣ ጥላቻ ፍቅርን፣ አድሎ እኩልነትን፣ ሃገራዊ ክህደት ሃገር መውደድን፣ ባንዳነት አርበኛናትን ለዘላላሙ ቀብረው የሄዱበት የሃገራችንና  የሰው ልጆች ታሪክ የለምና የወያኔን አይቀሬ ሞት ለመተንበይ  ልዩ ጥበብ አያሻንም። ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን በዘረፋና በጥላቻ  የደነዘዘ ህሊና ያዳበሩት የወያኔ  ባለስልጣናትም ያውቁታል። ያለእኔ  ጀግና የለም፣ ያለእኔ  አልሞ  ተኳሽ የለም በሚል እብሪት በመጻደቅ የሚታወቁት ወያኔዎች በመቶ ሽዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ተከበው፣  በታንክ በአይሮፕላን በሚሳይል ታጅበው ከሚኖሩበት ቤተመንግስትና ቪላዎች ውስጥ ብርክ እንዲይዛቸው ያደረገው ለመሆኑ፣  ሳር ቅጠሉ ግንቦት ሰባት እየመሰላቸው ሲበረግጉ እንደሚያመሹ፣  የግንቦት ሰባት አባላት እያሉ ከድርጅታችን ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች እያሰሩ ሲያሰቃዩ ፣  ከምላሳቸው ላይ ግንቦት 7  የሚል ስም ተፈናጦባቸው  እንደሚውሉ በራሳቸው ሚድያ  ወያኔዎች ራሳቸው እያሳዩን እያስደመጡን ነው። ከዚህም አልፎ በዚህ አንድ አመት ውስጥ  የህዝባዊ ሃይሉን መሪዎች በመግደል ድርጅቱን ለማኮላሸት ይቻላል በሚል ወያኔ የላካቸው ነፍሰ ገዳዮችና ድርጅቱን ከውስጥ ለመቦርቦር ያሰማራቸው ሰርጎገቦች ተራ በተራ ተልእኳቸው እየከሸፈ በህዝባዊ ሃይሉ እጅ እየወደቁ ወይም ተልእኳቸው እንደማይሳካ ሲረዱ እየፈረጠጡ ወደ ወያኔ ሲመለሱ አይተናል።
ያለፈው አንድ አመት ተመክሯችን ስለወያኔ  ብቻ ሳይሆን ስለራሳችንም ጥንካሬና  ድክመት ብዙ ነገሮች ያስተማረን ኣመት ነው። የቀደምቶቻችን የጀግንነት የአርበኛነት ቅርስ በመላ ህዋሳቸው የተሸከሙ  ለኢትዮጵያ እና  ለህዝቧ ሲሉ ደማቸው ለማፍሰስ ውድ ህይወታቸውን ለመሰዋት ወደኋላ የማይሉ ቆራጥ ብቻ ሳይሆኑ አርቀው የሚያዩ  በርካታ ልጆች  ሃጋሪቷ ያሏት መሆኑን ያረጋገጥንበት አመት  ነው።  በሌላ በኩል ደግሞ  ድርጅታችን የኢትዮጵያን ህዝብ ብቸኛው የመንግስት ስልጣን ባላቤት የማድረጉን ታሪካዊ ራእዩን ለመሳካት የሚያደረገው ትግል ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ጋር የሚደረግ እንደሆነ  በሚገባ  የተረዳነው  በዚሁ የአንድ አመት የድርጅታችን እድሜ  ነው። ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል ወያኔ በማህበረሰባችን ውስጥ ከዘራቸውና የሃገሪቱን ዜጎች እንዲበክሉ ካደረጋቸው የዘረኛነት የአድሎ  ከህዝብና  ከሃገር ጥቅም በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም፣ የሱሰኛነትና የሙስናና ሌሎችም አደገኛ ባህሎች ጋር ነው።
ህዝባዊ ሃይሉ ደግሞ  ደጋግሞ  እንደገለጸው ትግላችን አንድ መንግስታዊ ስርአት ወድቆ ሌላው የመንግስት ስርአት በመጣ ቁጥር የህዝብ ተስፋ እየጨለመ  “አዲስ ከመጣው ስርአት ያላፈው ያረጀ ስርአት በግፈኛነቱ በዘራፊነቱ ያነሰ ነበር” የሚል የግፈኛና የዘራፊ ስርአቶች ንጽጽር ላይ የቆመ አሳዛኝ የህዝብ ህይወት እንዲያበቃ ነው። ደርግን ያየ የአጼውን ስርአት እንከኖች ረስቶ ንጉሱ ይሻሉን ነበር ያለበት፣ ወያኔን ያየ የደርግን አስከፊ ዘመን ረስቶ መንጌ በስንት ጣሙ ያለበት አሳዛኝ ሁኔታ ከወያኔ መውደቅ በኋላ በሃገራችን እንዳይደገም ነው ትግላችን። የኢትዮጵያ ህዝብ የውድ ልጆቹን ህይወት ገብሮ ወያኔን በማስወገድ የሚያመጣው ስርአት ከወያኔ ብሶ ህዝብ ወያኔ ማረኝ የሚልበትን ቅስም ሰባሪና አዋራጅ የታሪክ ቅጥልጥሎሽ  እንዳይቀጥል ማድረግ ህዝባዊ ሃይሉ የተመሰረተበት፣ አባላቱ መከራ ለመቀበልና መስዋእትነት ለመክፈል በረሃ የገቡበት ዋናውና ብቸናው ምክንያት ነው። ትግላችንን መራራ የሚያደርገው ከበሰበሰውና የአንድ ጀምበር የህዝብ ቁጣ ከታሪክ ቆሻሻ የመጠያ ስፍራ ከሚከምረው  የወያኔ ስርአት ጋር ብቻ ሳይሆን በወያኔ ቦታ የሚተካውን ስርአት ከአድሎና ከዘረኛነት ከዘረፋና ሃገራዊ ክህደት የጸዳ፣ ዳግም ለኢትዮጵያውያን ውርደትና እንግልት ምክንያት እንዳይሆን ለማድረግ ከራሳችን ጋር ሳይቀር የማያቋርጥ ትግልን ማድረግ የግድ ስለሚል ነው። ህዝባዊ ሃይሉ የአመጽ ትግል የሚያደርግ፣ የመሳሪያው ብዛትና  የሰራዊቱ ቁጥር እያደገ  የሚሄድ ሃይል መሆኑን ስለምንረዳ  ይህን ሃይል ገና ከጅምሩ ከብዙ እንከኖች እያጸዱ ማደራጀት ካልተቻለ  በሃገርና በህዝብ ላይ የሚመጣውን አደጋ  የህዝባዊ ሃይሉ አባላት ጠንቅቀው የተረዱት ሃቅ ነው። ይህ ግንዛቤ የሰራዊቱን አባላት በጥንቃቄ መመልመልን፣ ማሰልጠንንና መገንባትን የግድ የሚል ነው።
ይህ ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል እጅግ መራራ ነው። ታሪካዊ ስህተቶችን ላለመድገም የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ትግል የአካልና የመንፈስ ጽናትን፣ ሃቀኛነትን፣ ታማኝነትን፣ ጀግንነትን የሚጠይቅ ትግል ነው። የወያኔ ስርአት ከሃገር ግድያው በተጨማሪ ትውልድን ለመግደል ሆን ብሎ ያስፋፋቸው እኩይና ጎጂ ባህሎችና ልምዶች ምን ያህል ማህበረሰባችንን እንደጎዱት ህዝባዊ ሃይሉ ባላፈው አንድ አመት እድሜው በሚገባ የተረዳው ጉዳይ ሆኗል። ህዝባዊ ሃይሉ የሚመኘውን የኢትዮጵያ ትንሳኤና ተሃድሶ እውን ለማድረግ እነኝህ  ወያኔ ሆን ብሎ  ያስፋፋቸውን የባህልና የሞራል ብክለት ማጽዳት የግድ እንደሆነ የተረዳ አካል ሆኗል።
ትግላችን መደፍረስን መጥራትን፣ መንተክተክን መስከንን የትግሉ ሂደት አካል አድርጎ  የሚጓዝ ነው።   ትግሉ የሚልመጠመጠውን እንደቀስት ቀጥ ብሎ ከሚራመደው፣ በካፊያው የሚንቀጠ ቀጠውን ለዶፉ ደንታ ከሌለው፣ ዝናር በቅፌን ከምሩ ተኳሽ  የሚለይ መራራ ትግል ነው። ያለፈው አንድ አመት ይህን አስተምሮናል። ህዝባዊ ሃይሉ ትግሉ ቀላል ነው የሚል ከእውነታ ጋር ያልተያያዘ ቃል ለህዝብም ሆነ ህዝባዊ ሃይሉን ሊቀላቀሉት ለተዘጋጁት ወገኖቹ አይናገርም። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል ለተሰለፉ በሽዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ትግሉ የሚጠየቅውን የሞራል የስብእና ጥብቅነት፣ከፍተኛ  የሃገርና የወገን ፍቅር፣ ጥልቅ የሆነ የመስዋእትነት ፈቃደኛነት የሚጠይቅ መሆኑን ከማስረዳት አንቦዝንም። ህዝባዊ ሃይሉ ለህዝብ ቃል እንደገባው ከወያኔ  ጋር የምናደርገው ትግል በጥበብ በእውቀት በጥናት በጥንቃቄ የምናደርገደው ነው። ነጻነት ያለመስዋእትነት እንደማይሳካ ብናውቅም ለተራ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስንል በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የሃገሪቱን ውድ ልጆች በከንቱ የሚማግድ ጀብደኛ እንቅስቃሴ  አናደርግም። የውሸት ተስፋ  ህዝብን አንመግብም።  አይናችንን ከዋናው የኢትዮጵያና  የህዝቧ  ጠላት ከሆነው ከወያኔ ላይ አንስተን በሌሎች  ወያኔን እቃወማለሁ በሚሉ ሃይሎች ላይ አንተክልም። ከወያኔ ሌላ ወደ ጎን የምንዋጋው፣ የምንጨቃጨው አታካራ የምንገጥመው ምንም ሃይል አይኖርም። ወያኔን ለመምታት ህዝባዊ ሃይሉ የጨበጠው  ቡጢ ወገኖቻችን በፍቅር ለመጨበጥ የሚዘረጉ ጣቶች  እንዳሉት በጸረ ወያኔ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ  ከልባቸው ለመተባበር ለሚፈልጉ ሃይሎች ሁሉ ግልጽ እናደርጋለን።
ያለፈው አንድ አመት የመሰባሰብ የድርጅት ምስረታ  መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካና የወታደራዊ  ስልጠና የተሰጠበት፣ የድርጅት ማጠናከሪያና የማጥራት ሂደት የተካሄደበት ነው። በዚህ ረገድ የተሰራው ስራ አጥጋቢ ውጤት አስገኝቷል። ስልጠናው፣ ድርጅት ማጠናከሩና  ማጥራቱ ወደፊትም የሚቀጥል ነው። መጪውን አመት የተለየ የሚያደርገው ህዝባዊ ሃይሉ በህዝብ ላይ በሚደርሰው ግፍና ውርደት ከሚሰማው ከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት አልፎ ባላፈው አመት ሊደርስላቸው ያልቻለውን የሃገራችንን ግፉአን ህዝቦች መታደግ የሚችልበትን እርምጃዎች መውሰድ የሚችልበት አመት መሆኑ ነው። በዚህ የህዝባዊ ሃይላችን የአንደኛ አመት ምስረታ  ክብረ በአል ወቅት ወገንም ጠላትም በግልጽ እንዲያውቀው የምንፈልገው ይህን ሃቅ ብቻ ነው።
ውድመት ለዋናውና  ለብቸኛው የኢትዮጵያ ህዝብና  የኢትዮጵያችን ጠላት ለሆነው የወያኔ ገዥ ጉጅሌ!
ድል በወያኔ ግፈኛ ስርአት አበሳውን ለሚያየው የመላው የኢትዮጵያ  ህዝብ!
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል
Ginbot 7 Popular Force
www.ginbot7pf.org
Tel: +44 208 123 0056
email: pr@ginbot7pf.org

 POSTED BY SAMUALE TEWELDE

Monday, December 16, 2013

ነጋሪቱም ተጎስሟል፤ፋኖም ተሠማርቷል !!!

http://www.ginbot7.org/2013/12/15
ዛሬ ኢትዮጵያዊያን እያዩ ያሉት ውርደት ቃል የሚገልፀው አልሆነም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ዛሬ እየደረሰ ያለ ዓይነት ውርደት ደርሶባት እንደሆነ በታሪክ የተመዘገበ ነገርም ተፈልጎ አልተገኘም። ይሄ ለኢትዮጵያዊያን የጨለማ ዘመን ነው። በኢትዮጵያ እንዲህ ስደትና እንግልት፤ ሃዘንና ዋይታ የበዛበት ዘመን ታይቶ አይታወቅም።
በዚህ ግዜ በኢትዮጵያችን መንግስት ነኝ እያለ ራሱን የሚጠራ ቡድን አለ።ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ የገባችበት የውርደት አዘቅት ከባድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በህወሃቶች አዝማችነት ተስምቶ የማይታወቅ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ግፍ በዜጎች ላይ ይፈፀማል። የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ይዘው ግብረ ሶዶም እንዲፈፀምባቸው ያደርጋሉ፤ ሴቶች ልጆችን በጋራ ሁነው ይደፍራሉ፤ በተቀደሱ ስፍራዎች ገብተው ቅዱሱን ስፍራ ያረክሳሉ፤ ዜጎችን ከእርሻ ማሳቸው አፈናቅለው በገዛ አገራቸው መፃተኛ ያደርጓቸዋል። በአጠቃላይ ዜጎች በአገራቸው ተስፋ አጥተው ሃዘንተኛ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ተስፋ የቆረጡ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከምኖር ሂጄ ብሞት ይሻለኛል ብለው እግራቸው በመራቸው መንገድ ይሰደዳሉ። በእንዲህ ሁኔታ ከኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ250ሺህ በላይ ወጣቶች ይሰደዳሉ።ገሚሱ በየበርሃው በውሃ ጥማት ወድቆ ይቀራል፤ ገሚሱም የባህር አዞ ቀለብ ሁኖ ዱካው ይጠፋል። ከሞት ተርፈው በየአርብ አገራቱ የደረሱ ዜጎች በሰው ልጆች ላይ ሊደርስ የማይገባ ወንጀል ይፈፀምባቸዋል።ባንዲራቸውን በአንገታቸው እንደጠመጠሙ ሬሳቸው ሜዳ ላይ ተጥሎ የአርብ መሳቂያ መሳለቂያ ይሆናሉ። በዚህ ሰሞን በሳውዲ ዓረቢያ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ብሄራዊ ውርደት ሁኗል።
ይሄ በእንዲህ እንዳለ “መንግስት ነኝ “ እያለ ራሱን የሚጠራው ህወሃት በዜጎቹ ሲቃና መከራ እየቀለደ ይገኛል።አንድ ግዜ ዜጎቼን እያወጣሁ ነው ይላል፤ ሌላ ግዜ ደግሞ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ስለሆኑ አላውቃቸውም ይላል። ህወሃቶች በዚህ ብቻ አላበቁም በኢትዮጵያዊያኑ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ለማስቆም አዲስ አበባ በሚገኘው በሳውዲ እምባሲ ፊት ለፊት ሠላማዊ ሠልፍ እንዳይደረግ መከልከል ብቻ ሳይሆን ለሠላማዊ ሰልፍ የወጡ ዜጎችን የቻሉትን ያክል ወደ እስር ቤት አግዘዋል፤ ያገኙትን ሁሉ በቆመጥ እንዲደበደቡ አድርገዋል። የአካል ጉዳትም አድርሰዋል። ይሄን ሁሉ ግፍ የሚታደግ፤የህዝቡንም ሮሮ የሚሳማ መንግስታዊ አካል አልተገኘም። ዓለምም ፊቷን ያዞረችብን የሚመስል ሁኔታ ታይቷል።
ኢትዮጵያዊያን ቀና ብለን በኩራት በአርብ አገራት ጎዳናዎች ላይ የምንመላለስ ዜግች ነበርን። ስማችን ያማረ፤ ማንነታችን የተከበርን ዜጎች ነበርን። አረብ የሚያከብረን እንጂ እንዲህ የሚንቀንና የሚያዋርደን ዜጎች አልነበርንም። በዘመነ ህወሃት ግን ያ ሁሉ ክብራችን ተዋርዶ ዜጎቻችን እንደ ሌጦና ቆዳ በገንዘብ የሚሸጡ ሆኑ። በኢትዮጵያችን ላይ የነበሩ የቀድሞው ገዥዎች ምንም እንኳ ጨቋኞች ቢሆኑም ዜጎቻቸው በሌላ በማንም እጅ እንዲገላቱና እንዲዋረዱ የሚፈቅዱ አልነበሩም።በአንድ ወቅት አፄ ኃ/ስላሴን” ሠራተኛ ይላኩልኝ” ብለው የሳውዲው ንጉስ ሲጠይቋቸው “ለመሆኑ ምንድ ነው የምትፈልጉት መሃንዲስ ነው ወይስ ሃኪም “ብለው ይጠይቋቸዋል። አይ “እኛ የምንፈልገው በቤት ሠራተኛነት የሚያገለግሉንን ነው” ይላሉ አረቦቹ።አይ “እኛ ለቤት ሠራተኛ የሚሆን ዜጋ የለንም” ብለው መለስውላቸዋል።ለራሱም ሆነ ለወገኑ ክብር ያለው መሪ መልሱ እንዲህ እንጂ ሳውዲ ድረስ ሂዶ ዜጎቹን ለባርነት ለመሸጥ ሲዋዋል አይገኝም።
ደሳለኝ ኃ/ማሪያም ከስድስት ወር በፊት ሳውዲ ድረስ ገስግሶ ሂዶ የቤት ሠራተኞችን ለአረቦቹ ለመላክ ተዋውሎ መመለሱ የሚታወስ ነው። ይሄን ውል ሲዋዋል ግን ስለ ክፍያ፤ ስለ ዕረፍት ግዜ፤ በህመም ግዜ ምን ይሆናል የሚሉ መሠረታዊ ቁም ነገሮች በውሉ ውስጥ አልተካተቱም። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የኢንዶኔዥያ እና የፊሊፕልንስ መንግስታት ግን ምንም እንኳ ድሃ ብንሆንም ዜጎቻችንን የምንሰደው የታወቀ የክፍያ መጠን፤ የእረፍት ግዜ፤ የህመም ፈቃድ እነዚህንና ሌሎችን መሠረዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የተሟላ የህግ ድንጋጌ ሲኖራችሁ ነው። ይህን ህግ እስከምታበጁ ዜጎቻችን የእናንተ መጫወቻ እንዲሆኑ አንልክም ብለው እምቢ ማለታቸው ይታወቃል። ህወሃት መራሹ መንግስት ግን ስለውጪ አገር አኗኗር ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸውን ወጣት ልጆችን ያለ ምንም ህግ ከለላ አሳልፎ ለባእዳን ይሰጣል። ወጣት ሴቶችንና ወንዶችን ለግርድናና ለአሸከርነት የመላኩ የድለላ ሥራም ህወሃቶች ባቋቋማቸው ድርጅቶች ተካሂዶ ከዚህ ንግድ በተገኘው ገንዘብ ህውሃቶች ብዙ ገንዘብ አፈሱ። ወገኖቻችን ግን በአረቦች እጅ እንባቸውን በመዳፋቸው የሚሰፍሩ ሆነው ቀሩ።
ለዚህ ሁሉ መከራ እና ውርደት ያበቃን ምንድ ነው የሚል ርዕስም የሰሞኑ የመወያያ ርዕስ ሆኗል። የመከራውና የውርደቱ ምንጭ ፈርጀ ብዙ ቢሆንም ህወሃት ዋነኛው የችግሩ ምንጭ ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። በአጠቃላይ ግን ህወሃት መንግስት ነኝ ብሎ ሲያበቃ ዜጎችን ለመታደግ ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ እንኳ ቁጣቸውን እንዳይገልጹ መከልከሉ ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።ለዚህ ብሄራዊ ውርደትና መከራ በመጀመሪያ ደረጃ ሊጠየቅ የሚገባው ህወሃት እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። ህወሃት የኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆንን የመረጠ የጠባብ ዘረኞች ቡድን ነው። ዜጎቻቸን እንዲህ ላለው ጉስቁልናና ውርደት እንዲጋለጡ ያደረጋቸው ህወሃት መሆኑን መያዝ ለነፃነት ለሚደረገው ትግል አንዱ አካል ነው።
የተከበራችሁ ወገኖቻችን፤
በሳውዲ አረቢያ የሚሰቃዩ ዜጎችን በተመለከተ ህወሃቶች ምንም ተቆርቋሪነት ያሳዩበት ሁኔታ እንዳልታየ ታውቃላችሁ።ለወገን ተቆርቋሪነት ከህወሃቶች የሚጠበቅ ስላልሆነ እኛ አንደነቅም። አስቀድመው በገንዘብ አሳልፈው ለሸጧቸው ዜጎች ይቆረቆራሉ ብሎ መጠበቅ የህወሃቶችን ባህሪይ ካለመረዳት የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን ህወሃቶች ዜጎች ማኩረፊያ አገር እንኳን እንዳይኖሯቸው የሚያሴሩትን ሴራ ለመረዳት ካለመፈለግ የሚመነጭም ጭምር ነው። ወደ አረብ አገር የተሰደዱም ሆኑ በሌሎች አገር በስደት ላይ ያሉ ዜጎች በከፋቸው ግዜ ተመልሰው የሚገቡበት ሥፍራ አላቸው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ በኢትዮጵያ የለም። ጉራፈርዳ እና ቤንሻንጉል አገርህ አይደለም ተብሎ የተባረረ ወጣት መግቢያው የት ነው ? ከዚህ ሥፍራ ወደ ሳውዲ የተሰደደ ወጣት መመለሻው ወደየት ነው ? በዚያች አገር ድንጋይ ለመፍለጥ እንኳ የኢሕአዴግ አባል እንዲሆን በሚገደድበት አገር ምን አገር አለኝ ብሎ ነው የከፋው ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሰው? አዎን ኢትዮጵያዊያን ማኩረፊያ አገር የሌለን ከርታታ ዜጎች እንድንሆን ተደርገናል።አገር ያሳጡንም ህወሃቶች ናቸው እንጂ ሌላ ማንም አይደለም።
እንግዲህ ምን ይደረግ?
ይሄ ጥያቄ ግልጽና ቀላል መልስ አለው።አምርሮ መነሳት። ህወሃቶች በአዲስ አበባ ላይ ወንድ ልጅን አስገድደው ግብረ ሶዶም እንዲፈፀምበት ሲያደርጉ ሰምቶ “እነዚህ ምን ዓይነት አረመኔዎች ናቸው” ማለት ብቻ በቂ አይደለም።ለአረመኔ የሚገባውን ቅጣት ለመስጠት የአያቶቻችንን ጋሻና ጦር ማንሳት ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ነው። በሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ የቆየውን ውርደት እንምባ ብቻ የሚያስቆመው አይሆንም። እንዲህ የአረብ መቀለጃ የሆነውን ማንነታችንና ክብራችንን አስመልሰን አንገታችንን ቀና አድርገን በአርብ ጎዳናዎች ላይ እንደቀድሞው ዘመን በኩራት እንድንመላለስ የአያቶቻችንን ትጥቅ ከተሰቀለበት አውርደን መታጠቅ ግዴታችን ሁኗል።
ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ውስጥ ያለን ኢትዮጵያዊያን በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ውርደት ብሄራዊ ውርደት ነው እንላለን። ከዚህ በላይ ሌላ ብሄራዊ ውርደት የለም። ለዚህ ውርደት ያደረሰንም ህውሃት ነው። ህወሃት እስካለ ድረስ ብሄራዊ ውርደታችን ይቀጥላል እንጂ አይሻሻልም። እኛ የሚደርስብንን ውርደት ለማስቆም አምርረን ተነስተናል። እኛ እንዲህ ተዋርደን መኖርን ከቅድሞዎቹ ኩሩዎች አያቶቻችን አልተማርንም።እኛን ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ህወሃቶች አንገታችንን አስደፍተው አዋርደው አይገዙንም። አያቶቻችን ለነፃነታቸው እና ለአገራቸው ክብር ሲሉ በቆሙበት በጀግኖች ሥፍራ ለመቆም መንገዱን ጀምረናል። ከእንግዲህ ወዲያ ከዚህ ጉዞ የሚያቆመን ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል የለም። ለእኛ ነጋሪት ከተጎሰመ ቆይቷል እኛ የነጋሪቱን ድምፅ በሰማን ግዜ ሳናቅማማ ተነስተናል።
እናንተስ ሳትቅማሙ ለመነሳት የነጋሪቱን ድምፅ ሰምታችኋል ? ከወደ ሳውዲ የተሰማው ያ የሲቃ ጩኸት፤ ያ ሮሮ፤ ያ እንምባ አስደንጋጩ የነጋሪት ድምፅ ነው። ከዚህ ድምፅ በኋላ ፋኖ ይሠማራል እንጂ አያለቅስም።ማልቀስ የናቁንና ያዋረዱን እንዲያከብሩን አያደርግም። ነጋሪቱ ከተጎሰመ በኋላ አገሬን፤ ክብሬን የሚል ተነስቶ ያያቶቹን ጋሻና ጦር ያነሳል እንጂ እንዲያው ዝም ብሎ አያጉረመርምም።አገር ተዋርዳ፤ ህዝብ ተበደሎ ዝም ብሎ ተንጋሎ የሚተኛ ካለ ይህን ብሄራዊ ውርደት ካመጡ ቡድኖች በምን እንደሚለይ ራሱን ይጠይቅ። አበቃን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!!
  POSTED BY SAMUALE TEWELDE

Sunday, December 15, 2013

Ethiopia most restrictive Sub Saharan Country, Freedom House reports 2013

http://www.freedomhouse.org/report/freedom-net/freedom-net-2013
Ethiopia has one of the lowest rates of internet and mobile telephone penetration in the world, as meager infrastructure, a government monopoly over the telecom sector, and obstructive telecom policies have notably hindered the growth of information and communication technologies (ICTs) in the country. Despite low access, the government maintains a strict system of controls over digital media, making Ethiopia the only country in Sub-Saharan Africa to implement nationwide internet filtering. Such a system is made possible by the state’s monopoly over the country’s only telecom company, Ethio Telecom, which returned to government control after a two-year management contract with France Telecom expired in December 2012. In addition, the government’s implementation of deep-packet inspection technology for censorship was indicated when the Tor network, which helps people communicate anonymously online, was blocked in mid- 2012.
Internet Freedom
Prime Minister Meles Zenawi, who ruled Ethiopia for over 20 years, died in August 2012 while seeking treatment for an undisclosed illness. Before his death was officially confirmed on August 20th, widespread media speculation about Zenawi’s whereabouts and the state of his health prompted the authorities to intensify its censorship of online content. A series of Muslim protests against religious discrimination in July 2012 also sparked increased efforts to control ICTs, with social media pages and news websites disseminating information about the demonstrations targeted for blocking. Moreover, internet and text messaging speeds were reported to be extremely slow, leading to unconfirmed suspicions that the authorities had deliberately obstructed telecom services as part of a wider crackdown on the Ethiopian Muslim press for its coverage of the demonstrations.
In 2012, legal restrictions on the use and provision of ICTs increased with the enactment of the Telecom Fraud Offences law in September,1 which toughened a ban on certain advanced internet applications and worryingly extended the 2009 Anti-Terrorism Proclamation and 2004 CriminalCode to electronic communications.2 Furthermore, the government’s ability to monitor online activity and intercept digital communications became more sophisticated with assistance from the Chinese government, while the commercial spyware toolkit FinFisher was discovered in Ethiopia in August 2012.
Repression against bloggers, internet users and mobile phone users continued during the coverage period of this report, with at least two prosecutions reported. After a long trial and months of international advocacy on behalf of the prominent dissident blogger, Eskinder Nega, who was charged with supporting a terrorist group, Nega was found guilty in July 2012 and sentenced to 18 years in prison.
Read Freedom House reports 2013, Full report about Ethiopia
Read Freedom House reports 2013, Full Report
Source:  http://www.freedomhouse.org/


ሁለገብ- ትግል – ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የምንጋራው የትግል ስትራቴጂ

http://www.ginbot7.org/2013/12/14
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄም በኔልሰን ማንዴላ ዜና እረፍት የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ መግለጫ ያወጣ ቢሆንም የትግል ተሞክሯቸው ለአገራችን ስላለው ጠቀሜታ ተጨማሪ ቁም ነገሮችን ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል።
ኔልሰን ማንዴላንና የትግል ጓዶቻቸው መሣሪያ እስከማንሳት ያደረሳቸው የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ አገዛዝ ዋነኛው መገለጫው የባንቱስታን ሕግ ነበር። በዚህ ህግ መሠረት ደቡብ አፍሪቃ ዘርን መሠረት ያደረጉ አስር “ባንቱስታ” የተሰኙ “ራስ ገዝ” ግዛቶች ተቋቁመው ነበር። ያኔ በደቡብ አፍሪቃ አገዛዝ ሥር በነበሩ የደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ደግሞ ሌላ አስር ባንቱስታዎች ነበሯቸው። በእያንዳንዱ ደቡብ አፍሪቃዊ መታወቂያ ባንቱስታው እንዲገልጽ ህጉ ያስገድዳል። የአንዱ ባንቱስታ ነዋሪ ያለልዩ ፈቃድ ወደሌላው ባንቱስታ መሄድ አይችልም። ከዚህም ሌላ ለነጮች ብቻ በተከለሉ ቦታዎች ጥቁሮች ለሥራ ካልሆነ በስተቀር ለሌላ ማናቸው ተግባር እንዳይገኙ ህጉ ያዛል። አፓርታይድ የደቡብ አፍሪቃ ዜጎችን በየዘር ክልሎቻው ውስጥ አጉሮ አገራቸውን እስር ቤታቸው እንዲሆን አደረገው። ይህንን ለመቃወም ኔልሰን ማንዴላ እና የወቅቱ ታጋዮች በመጀመሪያ ሰላማዊ ትግልን ሞከሩ፤ ያ አላዋጣ ሲል መሣሪያ አነሱ።
በአሁኑ ሰዓት ባንቱስታን መሰል የክልል አስተዳደር ያለው በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ልክ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ እንደነበረው ሁሉ የኛም መታወቂያዎች ዘራችንና ክልላችንን ይገልፃል። በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ እንደነበረው ሁሉ እኛም ከክልላችን ውጭ ተንቀሳቅሰን መሥራትና መኖር አንችልም። ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ እና ከደቡብ ክልሎች ተፈናቅለው ለጎዳና ኑሮ የተዳረጉት የአማራ አርሶ አደሮች የዚህ ፓሊሲ ሰለባዎች ናቸው።
ኔልሰን ማንዴላ እና ድርጅቱ ኤ. ኤን. ሲ. በሰላማዊ ትግል ብቻ አፓርታይድን ማስወገድ እንደማይቻል የተገነዘቡት ከስዊቶ እልቂት ነው። በስዊቶ እልቂት 176 ዜጎች እንደተገደሉ ይነገራል። እኛ አገር ብዙ ስዌቶዎች አሉ። በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ እና በሶማሊያ የደረሱት እልቂቶች እያንዳንዳቸው የስዌቶን እልቂት ያክላሉ። በዚህም ላይ በሰቲትና በሁመራ የተደረገው ስልታዊ የዘር ማጥራት፤ የወጣቶች ያላባራ ስደት የዚሁ ፓሊሲ አስከፊ ውጤቶች ናቸው።
ሰላማዊ ትግል ብቻውን የደቡብ አፍሪቃ ዘረኛ አገዛዝን ማስወገድ አልቻለም። ሰላማዊ ትግል ብቻውን ወያኔ በአገራችን ላይ የጫነብን ዘረኛ አገዛዝ እንዲያበቃ ማድረግ ይችላል ብሎ ማመን አዳጋች ነው። ስለዚህም ነው ማንዴላ እንዳደረገው ሁሉ ግንቦት 7 ም ሁለገብ ትግልን እንደ ትግል ስትራቴጄ ለመያዝ የተገደደው።
ሁለገብ ትግል ሕዝባዊ አመጽ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አጣምሮ መያዝ ይጠይቃል። ሁለገብ ትግል መጨከንን ያም ሆኖ ለእርቅ አንድነት ለሀገር እና ለወገን የጋራ ጥቅም መሥራትን ይጠይቃል። ሁለገብ ትግል ዘረኝነትን በጽናት የመታገል ሆኖም ግን ይቅር ባይ መሆንን ይጠይቃል።
ግንቦት7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁለገብ የትግል ስትራቴጂን በአማራጭነት ሲወስድ ከወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ሥርዓትን ለመለወጥ የነበረውን ፍቱንነት በጥልቀት በማጤን ነው።
ዘላለማዊ እረፍት ለኔልሰን ማንዴላ
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢህአዴግ ከብሔር “ተኮር” ተቃዋሚዎች ጋር ሊሸማገል ነው

ኢሳያስ ወደ ኢጋድ እየተሽኮረመሙ ነው
eprdf to reconcile
ኢህአዴግ በብሔርና በክልል ደረጃ ከተደራጁ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱት ቅድሚያ በመስጠት ለመደራደር የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ በማመቻቸት ላይ መሆኑን የጎልጉል ምንጮች ገለጹ። ምንጮቹ እንደጠቆሙት ኢህአዴግ ለዚህ ተግባሩ ወዳጅ ጎረቤት አገሮችን፣ አንጋፋ የጎሳ መሪዎችንና ያፈገፈጉ የቀድሞ ተቃዋሚ መሪዎችን እየተጠቀመ ነው።
ህወሃት አሁን በአገሪቱ ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋ የሄደው አለመረጋጋት እንዳሳሰበው የጠቆሙት የኢህአዴግ ሰው ድርጅቱ እርቅ ላይ ከመቼውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ስትራቴጂ መንደፉን አመልክተዋል።
“ከውጥረት ለመውጣት ወይም ውጥረትን ለመቀነስ” በሚል ኢህአዴግ ትኩረት ሰጥቶ የጀመረው አዲሱ የ”ሰላም” መንገድ ህብረ ብሔር ድርጅቶችን ያላከተተበትን ምክንያት አልተብራራም። ይሁን እንጂ ከኢህአዴግ ባህሪ አንጻር አቋሙ ሊቀየር የሚችል መሆኑን አልሸሸጉም።
ለድርድር የተመረጡትን ብሔርና ክልል “ተኮር” ድርጅቶች ይፋ ማድረግ ለጊዜው እንደሚቸግራቸው ምንጮቹ ተናግረዋል። በድፍኑ ግን በተለይ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ክልልና ምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የነጻ አውጪና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶች በማዕቀፉ ውስጥ እንዳሉ አመላክተዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጪ ኢንቨስተሮች ፍሰት መቀነሱ፣ ገብተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ድርጅቶችም ከጸጥታና መሰል ችግሮች አገር ለቀው ወደመውጣቱ ላይ በመሆናቸው፣ አገሪቱ ውስጥ ያለው የስራ አጥነት ችግር እየተወሳሰበ መሄዱና ድህነት በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ መስፋቱ ህወሃቶችን እንዳሳሰባቸው ያስታወቁት የጎልጉል መረጃ ሰጪዎች “የኢህአዴግ አቻ ፓርቲዎችም ለህወሃት ያላቸው የአገልጋይነት መንፈስ እየተመናመነ መሄዱ ዋንኛው የህወሃት ጭንቀት ነው” ብለዋል። በዚህም የተነሳ እርቅ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ነው።
ህወሃት ባደራጃቸው የብሔርና የጎሳ ድርጅቶች ጥላ ስር ለይስሙላ ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ ከሚባሉ ክልሎችና ዞኖች “እውነተኛ ውክልና አለን” የሚሉ ብሄርን፣ ክልልንና ዞንን መሰረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ለማካሄድ የታሰበው ድርድር ተግባራዊ ከሆነ አተገባበሩ እንዴት ሊሆን እንደሚችልም ምንጮቹ አላብራሩም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ኦህዴድንና ኦነግን ለማስማማት ተካሂዶ በነበረው ንግግር ኦነግን ወደ ኦህዴድ ለማጠቃለልና ለኦነግ ስልጣን ለማጋራት የታቀደው እቅድ መክሸፉን አስታውሰዋል።
መረጃ ሰጪዎቹ አያይዘው እንደተናገሩት በቀዳሚነት በተለይ ከሶስት ክልልና ብሔር “ተኮር” ድርጅቶች ጋር ኢህአዴግ ለማከናወን የሚፈልገው እርቅ በክልሉ ወይም በዞኑ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን መሪዎች እጁን ዘርግቶ እስከመቀበል የሚያደርሰው ነው። ቀጥለው ሲያስረዱም ሙሉ አስተዳደራዊ ስልጣን እስከመስጠት ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።
ህወሃት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ አገሪቱን አሳንሶ አዳክሞና ቆራርጦ የማቀራመት ዓላማ ስላለው ምን አልባትም በደቡብ ክልል አዲስ ክልል ሊወለድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ከምንጮቹ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
Isaias-Afwerki-in-Kenya2
ኢሣያስ ከደቡብ ሱዳን መሪ ሳልቫ ኪር ጋር
በማስታረቁ ስራ ላይ የተሰማሩትን ማንነት መግለጽ ለጊዜው አግባብ አይደለም በማለት ዝምታን የመረጡት የኢህአዴግ ሰዎች እርቅ በመላው አገሪቱ እንደሚያስፈልግ አብዛኛው ካድሬና የበላይ አመራሮች ምኞት መሆኑን ጠቁመዋል። ዋናው ቁልፍ ያለው በህወሃት እጅ በመሆኑ ክልሎችን ቀደም ሲል ያስቀየመ አካሄድ በመሆኑ በአሁኑ እርቅ አካሄድ ላይ የክልል ከፍተኛ ባለስልጣኖችም እንደተሰማሩበት ተመልክቷል። ሰሞኑን ግንቦት 7 የፍትህና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ኢህአዴግ ለሶስት ጊዜ ያህል የእርቅ ጥያቄ እንዳቀረበለት መግለጹና ኢህአዴግም በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በኩል ግንቦት 7ን የመታረቅ እቅድ እንደሌለው በመግለጽ ጉዳዩን ማጣጣሉ ይታወሳል።
ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመሸምገል በይፋ ማስታወቋ፣ ኳታርም ቀደም ሲል በተመሳሳይ ለእርቅ ላይ ታች ስትል መቆየቷ የሚታወስ ነው። የሁለቱም አገራት የሽምግልና ሩጫ ምን ውጤት እንዳስመዘገበ የሚታወቅ ኦፊሳላዊ መረጃ ከየትኛውም ወገን አልተደመጠም። ይልቁኑም ህወሃትና ሻዕቢያ አንዱ የሌላውን ባላንጣ በማደራጀት ስራ ላይ መጠመዳቸው ነው በይፋ እየተነገረ ያለው።
Isaias-Afwerki-in-Kenya1
የኬኒያው መሪ ዑሁሩ ኬኒያታና ኢሣያስ
በሌላ በከል ደግሞ ኢጋድንና የኢጋድ አገራት መሪዎችን በይፋ ሲዘልፉ የነበሩት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰሞኑን በሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ተከትሎ አዳዲስ መረጃዎች እየተሰሙ ነው። ከኢጋድ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በይፋ ለማደስ እየሰሩ መሆናቸውም ተነግሯል። ኤርትራ በተባበሩት መንግስታት የተጣለባት እቀባ እንዲነሳላት አጠንክራ እየተከራከረች ባለችበት ወቅት ላይ ሆና ኢጋድን በወጉ ለመወዳጀት ወስናለች መባሉ ወሬውን ሚዛን የሚደፋ እንደሚያደርገው በርካቶች ይስማሙበታል።
ኢህአዴግ በቀጠናው ብሎም በኢጋድ ውስጥ ባለው ተሰሚነት የተነሳ መድረኩ ሻዕቢያንና ወያኔን በማገናኘት ለማሸማገል ለሚደረገው ጉዞ የመጀመሪያው ርምጃ እንደሆነ ከግምት በላይ የሚናገሩም አሉ። ከካርቱሙ ጉብኝት በኋላ በኬኒያ 50ኛ ዓመት የነጻነት በዓል ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጉዳዩ ላይ ከቀጣናው አገራት ጋር እንደሚመክሩበት በመግለጽ ጉብኝታቸውን ከዚሁ ጋር የሚያይዙ አሉ። ይህን አስመልክቶ ግን ከየትኛውም ወገን በገሃድ የተሰጠ መግለጫ ግን የለም።


በአዲስ አበባ ከ600 በላይ አባዎራዎች ቤታቸውን በ3 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ቀጭን ትዕዛዝ ተላለፈ




የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ደሃ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ ቦታቸውን እየወሰዱ ነው

በአዲስ አበባ ከ600 በላይ አባዎራዎች ቤታቸውን በ3 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ኢሳት ቴሌቭዥን ዘገበ። እንደ ቲቪው ዘገባ ትእዛዙን የሰጠው የቦሌ ክፍለከተማ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ እስከ ማክሰኞ ቤታቸውን ለቀው ካልወጡ ፣ አፍራሽ ግብረሀይል በጉልበት እንደሚያፈርስባቸው አስታውቋል።
“በሶስት ቀናት ውስጥ የት እንሄዳለን?’ ሲሉ የሚጠይቁት ነዋሪዎች ፣በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚታየው የቤት ኪራይ መጨመር አስግቶናል ብለዋል። ሜዳ ላይ እንዃ እንዳንወድቅ ሜዳውም እየታረሰ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገልጸዋል ሲል ዘግቧል።
በተያያዘ ዜናም ኢሳት በዜና ዘገባው በኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ባለስልጣናት በስልጣናቸው ደሀ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ ቦታዎቻቸውን እየወሰዱባቸው ነው ሲል ዘገበ። ነዋሪዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው አርሶአደሮች በጉልበት መሬታቸውን እየተቀሙ ለበለጠ ድህነት እየተጋለጡ መሆኑን አስታውቋል። ከተቀሙት አርሶ አደሮች መካከል በሰበታ ነዋሪ ከሆኑት አንዱ ሲናገሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት የአቶ ደምሴ ቡላ ባለቤት መሬታቸውን በጉልበት እንደነጠቁዋቸውና ክስ ሲመሰርቱም እንዳሳሰሩዋቸው ተናግረዋል ያለው ኢሳት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ቤት ሰርተው ይኖሩ ነበሩ ሰዎች ቤቶቻቸው ከፈረሱባቸው በሁዋላ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ይታወቃል ሲል የዜና ዘገባውን አጠቃሏል።
Ze-Habeshahttp://www.zehabesha.com/